ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ኩርባ ከተማ መነሻውን ያደረገ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ባጋጠመው የመገልበጥ አደጋ የ25 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
ዛሬ ከጥዋቱ 12 ሰዓት ከኩርባ ከተማ ተነስቶ ወደ ደሴ ከተማ ሲጓዝ የነበረው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3-32917 የሆነ በመጓዝ ላይ እያለ በግምት ከኩርባ ከተማ 9 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ልዩ ቦታው 04 ቀበሌ ሰጎራ ከተባለ አካባቢ የመገልበጥ አደጋ መድረሱን፤ የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው አራጌ ተናግረዋል፡፡
በአደጋውም የ25 ሰዎች ሞት፣ 14 ሰዎች ከባድ ጉዳት እንዲሁም 15 ሰዎች ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ከባድና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎችም በአቅራቢያው ከሚገኙ የደላንታና ደሴ ሆስፒታሎች ተወስደው፤ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ከዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ