የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እገዳን ተከትሎ ጫናን ለመቋቋም ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአትኩሮት እየተከታታለና ለጉዳዩ እልባት ይሆናሉ የተባሉ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ "በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ፕሮጀክቶች መቋረጡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሥራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አሳስቦኛል" ያለ ሲሆን፤ ለዚህም የመፍትሄ ሃሳቦችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ድጋፉ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ምክር ቤቱ በዘርፉ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት ለመቅረፍ በንቃት እየተከታተለ እንደሚገኝም አስታውቋል።
የምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የጽህፈት ቤቱ አመራሮች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮች ጋር ተገናኝተው በመምከር የፕሮጀክቶች ድንገተኛ መቋረጥ የሚያስከትሉትን ክፍተቶች ለመቅረፍ መወያየታቸውን በመጥቀስም፤ በመንግሥት በኩል አስፈላጊ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ መጠየቁን ገልጿል፡፡
"የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ በድንገት መቋረጡ በዚህ ድጋፍ ላይ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ይደገፉ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሚያገለግሏቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ በሚያደርጉት የልማት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ እና የዴሞክራሲ ሥራ ላይ የሃብት ክፍተት ፈጥሯል" ሲልም አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ይህንን በመገንዘብ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ቅድሚያ በመንግሥት በኩል አማራጭ ሃሳቦችን በማመንጨት መንግሥት በጥናት የተደገፈ ስልታዊ ድጋፍ እንዲሰጥ በቅድመ ውይይቶች ማሳሰቡን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በዘርፉ ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅእኖ መጠን በትክክል ለመረዳት አጠቃላይ የተፅዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ በጠየቀው መሰረት ግምገማ መከናወን መጀመሩንም አስታውቋል።
በግምገማውም ተጽዕኖ ላይ የወደቁ ተቋማት ብዛት፣ የፕሮጀክቶች አይነት፣ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ተመደቦ የነበረ በጀት፣ የተጠቃሚዎቸ (የተረጂዎች) ቁጥር እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶችን ጨምሮ ወሳኝ መረጃዎች በባለስልጣን መስሪያቤቱ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ገልጿል።
ግምገማው ከተጠናቀቀ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ ተወካዮች፣ የመንግሥት አካላት፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለጉዳይ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጎ፤ ምክክር በማድረግ ቀጣይ እና ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚሰበሰቡበት፣ እንዲሁም ወደ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክቷል።
ስለሆነም በዚህ ወሳኝ የተፅዕኖ ግምገማ ሂደት ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በንቃት እንዲተባበሩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥሪውን አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክር ቤቱ ሌሎች የልማት አጋሮች በዘርፉ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሸፈን እንዲረዳ የሚያደርጉትን ወሳኝ ድጋፍ በማጠናከር እንዲቀጥሉ ጥሪውን አስተላልፏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ