የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች እና የሰንበት ገበያዎች ላይ ፍቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የምርት አቅርቦትን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ መረጃ ጥናት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሰማ ጀማል፤ የጾም ወቅትን ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ፍቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በንግድ ስርዓቱ በምርቶቹ ላይ የዋጋ ተመን ማዘጋጀት እና በንግድ ተቋማት ላይ በአስገዳጅነት እንዲተገበር ማድረግ እንደማይቻል የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን በሰንበት ገበያዎችና በመንግሥት በተገነቡ የገበያ ተቋማት ላይ የምርት ዋጋ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ጤፍ በ12 ሺሕ 500፣ ዘይት እስከ 1 ሺሕ ብር፣ ሽንኩርት 55 ብር እንዲሁም ቲማቲም በ30 ብር እንዲሸጥ ስለመደረጉ አስረድተዋል፡፡

አክለውም በምርቶች ላይ አላስፈላጊ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው ለቢሮው በቀረቡ ቅሬታዎች ማወቅ መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህ ድርጊት ላይ በተሳተፉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የተወሰደበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ወቅቱ ምርት ወደ ገበያ የሚቀርብበት በመሆኑም፤ በምርት አቅርቦት ላይ እጥረት እንደማይኖር ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት በአብዛኞቹ ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ ስለመኖሩ አንስተው፤ ነገር ግን አሁንም በቢሮ የሚካሄደው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ከዚህ ቀደም 197 የሰንበት ገበያዎች እንደነበሩ በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያስተውል ለቢሮ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችል አቶ ሙሰማ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ