የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ፤ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ንግግር የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂያቫ ተናግረዋል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ያደነቁ ሲሆን፤ ስጋቶች እንዳሏቸውም ገልጸዋል፡፡

ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በኢትዮጵያ የተደረጉት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ጠንካራ ርምጃዎች እና ጊዜ የሚወስዱ ቢሆንም፤ ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ እንደሚችሉ በመግለፅ ትዕግስት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ይህንን የዳይሬክተሯን ንግግር ተከትሎ አሐዱ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፤ "ንግግራቸው መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ያልተጣጣመ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

" 'ትዕግስት ያስፈልጋል' የሚለው የዳይሬክተሯ ንግግር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በዚህ ሰዓት እያሳለፉ የሚገኘውን ችግር ያላገናዘበ ነው" ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሽዋፈራው ሽታሁን ተናግረዋል፡፡

ያለፈው ዓመት 2024 የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (GDP) 8 ነጥብ 1 በመቶ እንደነበር የገለጹት የአይ ኤም ኤፍ ኃላፊ፤ "ይህም ከተጠበቀው 6 ነጥብ 1 በመቶ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የላቀ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የብር ምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን መፍቅደን ጨምሮ የተለያዩ የምጣኔ ሐብት ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወሳል።

ይህንን በሚመለከት ሙያዊ እይታቸዉን ያጋሩን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆንጠንጢኖስ በርኄተሰፋ በበኩላቸው፤ "የብር ምጣኔ በዋጋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና እንደሚያደረግ የሚጠበቅ ነው" ብለዋል፡፡

የውጭ ተቋማት በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሳተፋሉ የሚባሉትም ቢሆን፤ የባንኩን እና ኢኮኖሚን ለማዘመን የሚረዱ ጉዳዮች በመሆኑ ነገሮች እየተስተካከሉ ይሄዳል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አሐዱም "ስጋቶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?" ሲል ጠይቋል፡፡

ዶ/ር ቆንጠንጢኖስ ሲመልሱም "እንደዚህ ዓነት ቀውሶች መፍትሄ የላቸውም፡፡ ይልቅም መንግሥት ውሳኔዎቹን ማጤን አለበት" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአውሮፓዊያኑ 2022 የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት 33 ነጥብ 9 በመቶ የነበረ ቢሆንም፤ ባለፈው ዓመት ወደ 23 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ብሏል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በ2026 ወደ 13 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ሊል ይችላል ተብሎ ግምት ተሰጥቶበታል።

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከአንድ ወር በፊት እንደገለጸው ደግሞ፤ የዋጋ ግሽበት በሕዳር ወር መጨረሻ 16 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱን አስታውቆ ነበር።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ