ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቀድሞው በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል።

ተቋሙን ለአምስት ዓመታት የመሩት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሥራ ዘመናቸው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ማብቃቱን ተከትሎ፤ ላለፉት አምስት ወራት የእርሳቸው ምክትል የነበሩት ራኬብ መሰለ ተቋሙንን የመምራት ኃላፊነት በተጠባባቂነት ተረክበው መያዛቸው ይታወቃል።

Post image

ዛሬ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በምክር ቤቱ ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ብርሃኑ ላለፉት አስር ዓመታት በግል አማካሪነት እና ጠበቃነት እየሰሩ የቆዩ ሲሆን፤ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል።

በተጨማሪም አቶ ብርሃኑ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነታቸው እስከተነሱበት ጊዜ ደረስ፤ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕንድ አገር የማስተርስ ዲግሪያቸውን መቀበላቸውም በምክር ቤቱ ተገልጿል።

Post image

ምክር ቤቱም አቶ ብርሃኑ ተቋሙን ለመምራት በትምህርት ዝግጁነትና በሥራ ልምድ "ብቁ ሆነው የተገኙ" መሆናቸውን በመማመን፤ ሹመቱን በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮምሽነር በመሆን የተመረጡት አቶ ብርሃኑ፤ በጉባዔው ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ