ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በሚገኝ ቅንጡ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ ላይ በደረሰ ፍንዳታ አንድ ሰው ሲሞት አራት ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
ፍንዳታው ከክሬምሊን በሰባት ማይል ርቀት ላይ በሚገኘውና በሩሲያ ዋና ከተማ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘውን አሌዬ ፓሩሳ (ስካርሌት ሴልስ) ቅንጡ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ ሲሆን፤ "በአደጋው ከተጎዱት ውስጥ የዩክሬን ተገንጣዮች ይገኙበታል" ሲሉ የሩሲያ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
የፍንዳታው መንስኤ ምን እንደሆነ እስከአሁን ባይገለጽም፤ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በከባድ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
ይህንንም ተከትሎ የሩሲያ ባለስልጣናት የወንጀል ምርመራ መጀመራቸው ነው የተዘገበው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቀው ምስል በሕንፃው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የሚያሳይ ሲሆን፤ የሕንጻው የመስታወት መስኮቶች፣ በሮች እንዲሁም ጣሪያው በከፍተኛ ደረጃ መሰባበራቸውን ያሳያል።
በአደጋው ከባድ ጉዳት ከደረሰባው መካከል በዶንባስ የበጎ ፈቃደኞች ሻለቃ መስራች እና የዶንዬትስክ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አርመን ሳርኪስያን እንደሚገኙበት ዘገባዎቹ አመላክተዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የደረሰባቸው ጉዳት ከባድ የሚባል መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፤ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ተወስደው የድንገተኛ ሕክምና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገን ተገልጿል።
ይህ በሞስኮ ቅንጡ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የደረሰው ፍንዳታ "በጥንቃቄ የታቀደ የግድያ ሙከራ" ነው ሲል የሩሲያ መንግሥት ሚዲያ የዘገበ ሲሆን፤ "በአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ላይ ያነጣጠረ ነው" ብሏል።
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሩሲያ በሞስኮ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በተለይ እ.ኤ.አ. በ2024 በከተማው ውስጥ በሚገኝ የኮንሰርት አዳራሽ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ140 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ