ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያግዛል በማለት፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ አዲስ ለመመዝገብ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዳግም ምዝገባ ቢጠሩም 84 የሚሆኑት እንዳልተመዘገቡ ባለስልጣኑ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ "እነዚህ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ምዝገባ ያላከናወኑ የትምህርት ተቋማት ከዘርፉ በራሳቸው ፈቃድ እንደወጡ ይቆጠራል" ሲልም ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ዳግም ምዝገባውን ለማድረግ ለባለስልጣኑ ሰነዶቻቸው የላኩ 273 ተቋማት፤ በመመሪያው የተቀመጡ ሰነዶችን ሙሉ በሙሉ ያላሟሉ መሆኑን አስታውቋል።
ይህን በሚመለከት የሆፕ ኢንተርፕራይዝ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቦርድ አባል ዶክተር ተረፈ ፈየራ፤ "ተቋማቱ ያልተመዘገቡት ተግባራዊ ለማድረግ ከበድ የሚሉ መስፈርቶች እንዳሉና ተቋማቱም ይህንን ለሟሟላት ስላልተቻላቸው ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በማህበሩ ውስጥ የነበሩ 18 የሚሆኑት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዳግም ምዝገባው እንዳልተመዘገቡ የሚናገሩት ዶ/ር ተረፈ፤ መስፈርቶቹ ሊኖሩ የሚገቡና አስፈላጊ መሆናቸውን በማመን ነገር ግን ከባድ እና ለመተግበር አስቸጋሪ የሚሆኑ መስፈርቶች እንዳሉም ገልጸዋል።
ለዚህም ተቋማቱ የእግር ኳስ ሜዳ እና ክሊኒክን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው በመመሪያው መቀመጡን እንደምሳሌ ያነሱ ሲሆን፤ ሕንፃዎችን የሚከራዩ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሜዳውን ለማግኘት እንደሚቸገሩና "ይህንን ማድረግ እንደማይችሉ በማመን ከኢንዱስትሪዉ ራሳቸውን አግለዋል" ብለዋል።
"መመርያውን በማንበብ እና አለመቻላቸውን አውቀው የወጡ ተቋማትም ሊደነቁ የሚገባ ነው" ሲሉም አክለዋል።
አሐዱም ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ ናቸው የተባሉትን መስፈርቶች አስመልክቶ፤ ከከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለም። ምላሽ ባገኘን አፍታ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ