ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች የቴክኒክ ደረጃዎችን፣ የፍቃድ መስፈርቶችን እና የደህንነት እርምጃዎችን የሚያወጣ አዲስ መመሪያ መጽደቁን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታውቋል።
ባለስልጣኑ "ይህ እርምጃ የኃይል አቅርቦትን ጥራት ለማሻሻልና የኃይል መሙያ ጣቢያን ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው" ብሏል።
በባለስልጣኑ የኢነርጂ አቅርቦት እና ቁጥጥር ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ እንጂራ፤ የመመሪያውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ አዲሱ መመሪያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች የቴክኒክ ደረጃዎችን፣ የታሪፍ አወቃቀሮችን እና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቶችን ለመቆጣጠር ይጠቅማል።
በተጨማሪም ይህ ወደ ንፁህ ሃይል የሚደረገውን ሽግግር የሚደግፍ አስተማማኝ እና በደንብ የተስተካከለ አሰራርን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡
መመሪያው ተደራሽነትን ለማሳደግ በፈጣን መንገዶች በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እና በ120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የጭነት መኪኖች እና ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እንደሚገጠሙ ይገልጻል።
በተጨማሪም፣ ሁለቱንም አገልግሎት ሰጪዎችን እና ደንበኞችን ደህንነትን እና የአሰራር ደረጃዎችን ለመጠበቅ ተጠያቂ ያደርጋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ከ400 በላይ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያስመጡና እየገጣጠሙ መሆናቸውን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ተቋማቱ ሁሉም የኃይል መሙያ እንዳላቸው አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ