ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሩሲያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነትን አስመልክቶ ለሰጡት አስተያየት ዛሬ ሐሙስ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፤ በምላሿም ከትራምፕ ጋር ''መከባበር የተሞላበት የጋራ ንግግር'' ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የትራምፕን አስተያየት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ ''በተለይ አዲስ አካላትን አናይም'' ያሉ ሲሆን፤ ትራምፕ ማዕቀቦችን እንደሚወዱ እና ሩሲያም የሚሰጡትን መግለጫዎች በቅርበት እንደምትከታተል መናገራቸውን ኤፍ ፒ ዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ትሩዝ በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ካልተስማሙ፤ በሞስኮ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጣል ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ትራምፕ አክለውም ''ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ካልተስማማን ሩስያ እና አጋሮቿ ለአሜሪካ በሚያቀርቡት ማንኛውም ምርት ላይ ታክስ፣ ታሪፍ እና ማዕቀብ ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ ሌላ ምርጫ የለኝም'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አሜሪካ "ሩሲያን ለመጉዳት" እንደማትፈልግ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ "ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ሁልጊዜ ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው" አክለዋል፡፡
የሪፐብሊካኑ መሪ ትራምፕ ''በሩስያ እና በዩክሬን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ያለበት ጊዜው አሁን ነው'' በማለትም አፅንዖት ሰጥተዋል።
ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2022 ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በጦርነቱ ምክንያት አሜሪካን በጣለችባት ማዕቀቦች የንግድ ልውውጧ መቀዛቀዙ እየተነገረ ይገኛል።
በአውሮፓዊያኑ 2024 የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት አሜሪካ ከሩስያ የምታስገባው ምርት በ2021 ከነበረበት 29 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ወደ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ማለቱም ነው የተገለጸው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ