ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለጋዛ ማገገም ከማያስችላቸው ፈተናዎች አንዱ በ15 ወራት ጦርነት የተተዉ ፈንጂዎችን እና ሌሎች ያልፈነዱ ፈንጂዎችን ማጽዳት ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የግሎባል ጥበቃ ክላስተር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች የሰብአዊ ድርጅቶች ቡድን በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ፤ በጋዛ ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩት ፈንጂዎች 42 ሚሊዮን ቶን ከሚሆነው ፍርስራሹን ለማፅዳት ከ10 ዓመታት በላይ እንደሚፈጅ እንዲሁም 500 ሚሊዮን ዶላር ሊያስወጣ እንደሚችል ተገምቷል።
እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በሁለቱ ኃይሎች መካከል የነበረው ጦርነት ጋዛን 69 ዓመት ወደኋላ እንድትመለስ አድርጓታል ሲል አስታውቋል፡፡
በጋዛ የመጠለያ ቤቶችን ገንብቶ የማጠናቀቅ ሥራ ብቻ እስከ ፈረጆቹ 2040 ድረስ ዓመታት ሊወስድ እንሚችልም ተናግሯል፡፡
ለአስርት ዓመታት በዘለቀው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት የቅርብ ጊዜ ደም መፋሰስ የተቀሰቀሰው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሲሆን፤ ይህም የፍልስጤም ሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ጥቃት በመሰንዘር 1 ሺሕ 200 ገድለው 250 የሚጠጉ ታጋቾችን በወሰዱበት ወቅት ነው።
"እስራኤል በጋዛ ላይ ባካሄደችው ወታደራዊ ጥቃት ከ47 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያንን ገድላለች" ሲል የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ጥቃቱ መላውን የጋዛ ሕዝብ ከሞላ ጎደል ያፈናቀለ እና የረሃብ ቀውስ ያስከተለ ነው።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች ከእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ የተቹ ሲሆን፤ ዋሽንግተን በጋዛ ሃማስ፣ በሊባኖስ ሂዝቦላህ እና በየመን የሁቲ አማፅያንን ጨምሮ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖችን ለመከላከል አጋሯን እየረዳች ነው ስትል ድጋፏን አጠናክራለች።
ይህ እየተነገረ ባለበት ወቅት ከ15 ወራት በላይ በጋዛ ደም አፋሳሽ ጦርነት በተኩስ አቁምም ስምምነት ጋብ ይላል ተብሎ ቢጠበቅም፤ እስራኤል እየወሰደችው ባለው ወታደራዊ እርምጃ ምክንያት ጦርነቱ ዳግም እንደአዲስ ማገርሸቱ ተነግሯል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ