ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 116 ዓመት የሞላዉ የፌደራል ፖሊስ የአምስት ዓመት የለውጥ ጉዞን በሚመለከት ለሚዲያ አካላት ጉብኝት አካሂዷል።
የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ዕድሜዉን የሚዋጅ እና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ተቋም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የወንጀል መከላከል ሥራን በዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠር ሥራን እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።
"የሞባይል መተግበሪያ ጭምር በመስራት ወንጀልን ለመከላከል የለዉጡ ሥራ አንዱ ማሳያ ሆኗል" ሲሉም መቀመጫቸውን በሀገር ውስጥ ላደረጉ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች እና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ማዕከላዊ ዜጎች ይሰቃዩበት የነበረበት ሁኔታ መኖሩን የገለፁ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን ፖሊስ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ በተጠበቀ መንገድ የምርመራ ሥራ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከምክትል ኮሚሽነሩ የመክፈቻ ንግግር በኃላ ተቋሙ ባለፉት አምስት ዓመታት የሰራቸውን የለውጥ ሥራዎች በሚዲያ ተቋማት ጉብኝት ተደርጓል።
በተለይም የፌደራል ፖሊስ ከቴክኖሎጂ በመጠቀም እየሰራቸው ያሉ የደህንነት እና የክትትል ሥራዎችን እንዲሁም ዘመናዊ መገልገያ ተሽከርካሪዎች የጉብኝቱ አካል አድርጓል።
ከዛም ባለፈ በሰንዳፋ ከተማ በቅርቡ የተመረቀውን የፎረንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩት የምርምር የልህቀት ማዕከልን እና የኢንተርናሽናል ፖሊስ ሊደርሽፕ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክትን ጨምሮ የተለያዩ የተቋም የሪፎርሙ ሥራዎች ተጎብኝተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ