ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት 6 ወር ውስጥ በአዲስ አበባ የሚፈጸሙ ከባባድ ወንጀሎችን 42 በመቶ ያክል መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ከባድ ወንጀል የሚባሉት በሰው መግደል የሚጀምር ሆኖ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዘረፋ እና አካል ማጉደልን ጨምሮ ከ10 ያላነሱ የወንጀል ሁኔታዎችን ያካተተ መሆኑን የገለጹት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ናቸው።

Post image

እነዚህ ድርጊቶች በተወሳሰበና በረቀቀ መልኩ እንዳይገኙ ሆነው የሚፈፀሙ በመሆናቸው አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በጣም ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ የተለያዩ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና ህብረተሰቡም የማይተካ ሚና በመወጣቱ የከባድ ወንጀሎችን 42 በመቶ ያክል መቀነስ መቻሉን ለአሐዱ ገልጸዋል።

ወንጀልን መቀነስ ወይም ስጋት መሆኑን ማስቀረት ካልሆነ በስተቀር የትኞቹም ሀገራት ላይ ሙሉ ለሙሉ እንደማይጠፉ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፤ በወንጀል መከላከል እና በሌሎችም ሥራዎች ቀላል የማይባሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ጊዜያቶች በዚህ ደረጃ ባይሆንም የከባድ ወንጀል ድርጊት ቀንሶ እንደነበረ በመግለጽ በዘንድሮው ዓመት የተገኘው ውጤት ግን ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ወንጀልን ለመከላከልና እንዲቀንስ ለማደረጉ ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻሉ ጉልህ ሚና መጫወቱን መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ማርቆስ፤ የፖሊስን የዕለት ከእለት ከፍተኛ ድካም ከመቅረፍ እና ወንጀለኛው በቀላሉ በቁጥጥር ሥር የሚውልበትን መንገድ ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

በመሆኑም እንደ አዲስ አበባ ፖሊስ ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማ አለፍ ሲልም እስከ ጣቢያዎችና ወደፊት በቀጠና ደረጃ ሁሉ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

እንዲሁም "በሥራ ሂደቱ ላይ አጥፊ የፖሊስ አባሎችና አመራሮች ካሉ ኅብረተሰቡ በአቅራቢያ ከሚገኝ አመራር ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ፖሊስ ድረስ መጥቶ መረጃ በመስጠት ያሉት ችግሮች እንዲስተካከሉ ለማድረግ አስተዋጽኦውን መወጣት አለበት" ሲሉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ