ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ምዝገባ እና ሥነ-ምግባር አዋጅ 1162/2011 ለማሻሻል ከፓርቲዎች ጋር ውይይት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለያዩ የረቂቁ አንቀፀች ላይ ሀሳቦች እየሰጡ ይገኛል፡፡
ከአሐዱ ጋር ቆይታ የነበራቸው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አላማርው ይርዳው፤ "በአዋጁ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ በሚመለከት በአመራር ላይ እስከ 30 በመቶ ሴቶች መደረግ አለባቸው የሚለው ሀሳብ ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚደገፍ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ በቅርቡ ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ ከዘጠኙ ሥራ አስፈፃሚ አምስቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
"ነገር ግን ባለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ሴቶችን 20 እና 30 በመቶ በአመራር ላይ ማድረግ ይቻላል ወይ?" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
"በተለይም ሴቶች ካለባቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አንፃር በዚህ ደረጃ ሴቶች የፖለቲካ አመራር መደረግ አለባች ተብሎ በአወጁ ላይ መቀመጡ ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ ነው" ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ምርጫ ቦርድ እያሻሻለ በሚገኘው አዋጅ ላይ፤ 'በተለይም በምርጫ የሚወዳደር አንድ ፓርቲ ቢያንስ 20 በመቶ ዕጩዋቹ ሴቶች መሆን አለባቸው' ይላል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ በፖለቲካ አመራርነትም የሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ ብሎ ያመነውን 'ሴቶች በፖለቲካ አመራርነት ቢያንስ 30 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው' ሲል ያስቀምጣል፡፡
አሐዱም ለመሆኑ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተነሱ በተለይም ሴቶች በገዢ ፓርቲዎች ላይ ካልሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት የላቸውም የሚለውን ሀሳብ በሚመለከት ቦርዱን ጠይቋል፡፡
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ 'ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲ ላይ ሊሳተፉ አይችሉም' የሚል ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ሀሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ከሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በተያያዘ ይህ አስተሳሰብ መታረም ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ረቂቁ ገና ውይይት ላይ ባለበት ሁኔታ 'መሳተፍ አይፈልጉም' የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አስጋሪ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ሥነምግባር አዋጁ በተለይም ከሴቶች በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በሚያሳድግ መልኩ ማሻሻያ እንደተደረገበት ቦርዱ ገልጿል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ