ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር የመሰረታዊ ፍላጎቶችም አብሮ የሚጨምር በመሆኑ፤ የዜጎች የቤት ፍላጎት ከዚሁ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣቱን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት "በአሁኑ ሰዓት ያለው የህብረተሰቡ የቤት ፍላጎት እና የቤት አቅርቦት እድገት ንጽጽሩ የተመጣጠነ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ በስፋት በርካታ ቤቶችን መገንባት እና የግል ዘርፉንም ተሳታፊ ያደረገ የቤት ልማት ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ቀደም ሲል ከነበረበት የዝግታ ሂደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ሁኔታ በመፍጠን የችግሩ መንሰራፋት መንስኤ መሆኑን አንስተዋል።
"ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያማከለ የቤት አቅርቦት ሥራ መሰራት ደግሞ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተዳረሽ ያደርጋል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ጅምር ሥራዎች ስለመኖራቸውንም አብራርተዋል።
በከተሞች አካባቢ ብቻ ሳይሆን የገጠሩ ክፍልም የቤት አቅርቦት ልማት አካል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም እነዚህን ሥራዎች በማስተባበር እና በመምራት እየሰራ እንደሆነ ተናገረዋል፡፡
"የማህበረሰቡ የቤት ፍላጎትን በመንግሥት አቅርቦት ብቻ የሚሟላ አይደለም" ያሉም ሲሆን፤ ከግል ዘርፉ ጋር በጋራ በተሰራው ሥራም ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ዘርፍ መሆኑን አክለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጥያቄን ለመመለስ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር መስራት እና የግሉን ዘርፍ ማበረታታት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ