ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከኢትዮጵያ ሕዝብ 97 በመቶ የሚሆነው በአዮዲን የበለፀገ ጨው የማግኘት እድል እንዳለው የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
ከ2015 በፊት በኢትዮጵያ ያለው የአዮዲን እጥረት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ ችግሩን ለመፍታት በተሰራ ሥራ ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈፀም ሥራ አስፈፃሚ ሙላት ተስፋዬ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ከ2015 በፊት በአዮዲን የበለፀገ ጨው 5 በመቶ ብቻ የሚያገኝ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ 97 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በአዮዲን የበለፀገ ጨው የማግኘት እድል እንዳለው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባጠናው ጥናት መረጋገጡን ተናገረዋል።
ይህም በየሸቀጣሸቀጥ መደብሮችና ሱቆች ላይ በሚገኝ ጨው ላይ ተመርምሮ ቢያንስ አዮዲን አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለው ብቻ የተረጋገጠ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው አሳውቀዋል።
ነገር ግን የትኞቹ የጨው አይነቶች በደረጃው መሰረት ወይም መጠቀም የሚጠበቅባቸውን የአዮዲን መጠን በትክክል ተጠቅመዋል ከሚል ቁጥጥር አንፃር ክፍተት መኖሩን አክለዋል።
ሆኖም ግን በተለያየ መንገድ ገበያው ላይ በተጠና ጥናት 18 በመቶ የሚሆነው ጨው ያለው የአዮዲን መጠን ከደረጃ በታች መሆኑን በማንሳት፤ እንዲህ አይነት ክፍተት በሚፈጥሩት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቀዋል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ