ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ የቀረቡ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ቀሲስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እንዲሁም የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ክስ መስርቶ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም ተከሳሾቹ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ተከሳሾች በተለያየ መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ6 ሚሊየን 50 ሺሕ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለባንኩ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ማቅረቡም አይዘነጋም።
በዚህ መልኩ የቀረበውን ዝርዝር ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፤ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የሀሳብ ልዩነት ያቀረቡት አንደኛው ዳኛ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት የባንክ ሂሳባቸው በመገለጹ ብቻ የወንጀል ተግባሩ በስምምነት ተፈጽሟል ለማለት አያስችልም የሚል የሀሳብ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው ልዩነታቸውን አሳይተዋል።
በዚህም1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን ያቀረቡትን አራት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 21 መሰረት በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ እያንዳንዳቸው አራት፣ አራት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በዕርከን 17 መሰረት በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በ3 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የተወሰነውን የጽኑ እስራት ውሳኔን የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ እንዲያስፈጽም መታዘዙን ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ