ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ 627 አባወራዎች በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የተሰበሰበው ገንዘብ እንዳልደረሳቸው እና 'ይሰራላችኋል' የተባለው ቤትም እንዳልተሰጣቸው የተናገሩት ተፈናቃዮቹ፤ "ቃል ከተገባልን ውሰጥ ተግባራዊ የተደረገው ጥቂቱ ብቻ ነው" ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም "የተደረገው እርዳታ በቂ አይደለም" ብለዋል፡፡

"የመሬት መንሸራተቱን ተከትሎ አዲስ ወደ ተገነባልን መኖሪያ ቤት ከተሸጋግረን በኋላም እርዳታ የተደረገልን አንዴ ብቻ ነው፤ እሱም አጥጋቢ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ ለሚዲያዎች በመናገራቸው ምክንያት በዞኑ አስተዳደር ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

Post image

የመኖሪያ ድጋፍ የተደረገላቸው አባወራዎች ቁጥርም አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ አብዛኛው ሕዝብ በመጠለያ ውስጥ አመቺ ባልሆነ ስፍራ ላይ እንዳሉ አብራርተዋል።

በዚህም ምክንያት አሁን ላይ ምቹ ቦታ ላይ አለመኖራቸውን እና አሳሳቢ ችግር ላይ መውደቃቸውንም ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

አሐዱም ቅሬታ አቅራቢዎችን መሰረት በማድረግ የዞኑን የመንግሥት ኮምኒኬሽን መምሪያ ጠይቋል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ ገነነ እንዳሻው በምላሻቸው፤ ስለ ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከታቸው ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ኮሚቴዎች መሆናቸውን እና ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው በመግለጽ፣ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አሐዱም በኃላፊው ጥቆማ መሰረት፤ የኮሚቴውን ሰብሳቢ እና የዞኑ ደንና የአካባቢ ጥበቃ ልማት መምሪያ ኃላፊ ቦረና ቦላዶን ጠይቋል፡፡

በምላሻቸውም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን አንስተው፤ "በሚዲያዎች የሚሰራጨው መረጃ የዞኑን ገጽታ ለማበላሽት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

አክለውም በአደጋው ከ600 መቶ በላይ አባዎራዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ "ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ መኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸዋል" ሲሉ ጠቁመዋል። የትኛውም ተፈናቃይ እንዳልታሰረም ገልጸዋል፡፡

አሐዱም ቀሪ አባዎራዎች ያሉበትን ሁኔታን የጠየቀ ሲሆን፤ ሰብሳቢው በምላሻቸው ሌሎች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

"እነዚህም ተፈናቃዮች ምግብ፣ መድኃኒትና አልባሳት በየጊዜው በበቂ ሁኔታ እየተሰጠቻው ይገኛል" ነው ያሉት።

"ለአንድ ቤት ግንባታ ዝቅተኛ የተያዘው 600 ሺሕ ብር ነው" ያሉት ሰብሳቢው፤ ለእያንዳንዱ አባወራ 40 ቅጠል ባለቆርቆሮ ክዳን ቤት ተገንብቶ እንደሚሰጣቸውም አብራርተዋል።

አደጋውን ተከትሎም በርካታ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ጥረት ማድረጋቸው ቢገለጽም፤ በአንጻሩ የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተፈናቃይ ዜጎች በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ