ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ የቀረቡ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በተከሰሱበት ድንጋጌ ሥር የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ቀሲስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ሥራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እንዲሁም የኒሞና ንግድ ሥራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
የክስ መዝገቡም ከአፍሪካ ሕብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ በተለያየ መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ6 ሚሊየን 50 ሺሕ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለባንኩ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ነው።
በዚህ መልኩ የቀረበው ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፤ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ የሚጣራ መሆኑን ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።
ከዚህም በኋላ ተከሳኞቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ የአፍሪካ ህብረት ቅርጫፍ የባንክ ባለሙያዎችን አጠቃላይ ሦስት ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል መርምሮ በክሱ ዝርዝር የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ማረጋገጡን ጠቅሶ፤ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን ተከሳሾቹ ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን ጠቅሷል።
በዚህም በዛሬው ቀጠሮ 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ሲሆን፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የሀሳብ ልዩነት ያቀረቡት አንደኛው ዳኛ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት የባንክ ሂሳባቸው በመገለጹ ብቻ የወንጀል ተግባሩ በስምምነት ተፈጽሟል ለማለት አያስችልም የሚል የሀሳብ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው ልዩነታቸውን ማሳየታቸውን ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ተመልክቶ የቅጣት ውሳኔ ለመወሰን ለጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።