ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የገናንና የጥምቀት በዓልን ለማክበር እስካሁን ከ10 ሺሕ በላይ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር አስታውቋል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ቅድስት ልዑልሰገድ ከገና በዓል በፊት ሁለት ወር ቀድመው የገቡ መኖራቸውን በመጥቀስ፤ "አሁንም የጥምቀት በዓልን ለማክበር በመግባት ላይ ናቸው" ብለዋል፡፡
ወደ ሀገር የገቡት ዲያስፖራዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ለአሐዱ ገልጸዋል።
የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ቃልአብ ግርማ በበኩላቸው በዓለም ላይ 4 ሚሊዮን የሚገመት የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ "ወደ ሀገር ቤት እየገባ የሚገኘው የዲያስፖራ ቁጥር በቂ የሚባል አይደለም" ብለዋል።
አክለውም በየዓመቱ ከዲያስፖራው የሚገኘው 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ የተሻለ ገቢን ለማምጣትና ልማትን ለማፋጠን የተጠናከረ ሥራ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።