ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በያዝነው የ2017 ዓ.ም. የመጀመሪያው ስድስት ወራት፤ ለ1 ሚሊዮን 815 ሺሕ 800 ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ስልጠና በመስጠት እንዲደራጁ ማድረጉን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዴስክ ኃላፊ ብርሃኑ ፋንታዬ፤ ወጣቶች በሰለጠኑበት ሙያ ዕውቅና እንዲያገኙ እና ወደ ሥራው እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"የሴቶችና ማኅበራዊ የወጣቶች ዘርፍ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ካገዛቸው ወጣቶች መካከል 1 ሚሊዮን 300 ሺሕ ያህሉ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ገብተዋል" ብለዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም፤ በኢትዮጵያ ሥራ-አጥ ወጣቶችን ወደ የተለያዩ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ወጣቶቹ ተደራጅተው ሥራ የጀመሩባቸው ዘርፎች፤ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የቱሪዝም እና የኮንስትራክሽን ዘርፎች መሆናቸውም ታውቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ