ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰሞኑን ግለሰቦችና ቡድኖች ሃይማኖታዊ ቅራኔ እና ጥላቻ ሊፈጥሩ የሚችሉ በቪዲዮ የለቀቁትን አሉታዊ መልእክቶችን እና ተግባራትን በፍጥነት ለማረም በጽሕፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ እና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም ከእምነቱ ሥርዓት ባፈነገጠ መንገድ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የሌላውን እምነትና ሥርዓት በማንቋሸሽ፣ ክብረ ነክ ተግባራትን በመፈጸም፤ በተለይም በጥምቀት በዓል ታቦተ ሕጉ ላይ በመሳለቅ፤ የኢስላማዊ አለባበስ መገለጫ የሆነውን ጀለቢያ በመልበስ ሙስሊሞች በመምሰል የትንኮሳ ስብከቶችና ዝማሬዎች በማቅረብ፣ የትንኮሳ አለባበሶች ጭምር በመጠቀም በማኅበራዊ ድረገጽ የለቀቁት አጫጭር ቪዲዮችዎች የእምነቱ ተከታዮችን ማስቆጣቱን አብራርቷል፡፡

"ይህ ዓይነቱ ተግባር በሀገራችን ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበር፣ በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን የሚሸረሽር ድርጊት" መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ በሁሉም ሃይማኖቶች የሚወገዝ የድፍረት ድርጊት በመሆኑ ይህን የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ፣ መጠየቅም መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ቡድን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሌሎችን መብትና ጥቅም በሚጻረር አግባብነት የሌለውና ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት የሚፈጽም ማንኛውም ሕገ ወጥ ተግባር በዝምታና ሊታለፍ እንደማይገባውም ገልጿል፡፡

በመጨረሻም ማኅበራዊ ድረገጾችን እና ሚዲያዎችን በመጠቀም የጥላቻ ንግግሮች፣ ትንኮሳዎችና ክብረ ነክ ድርጊቶች የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፤ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ከፍትሕ የጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቴሌቭዥን ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አያይዞም ይህ ዓይነቱን ተግባር ለመከላከል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሥርዐት ላይ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት እና ታቦት ላይ እየቀለዱ ቪዲዮ በመቀረፅ ቲክቶክ በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራታቸውን ተከትሎ፤ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቁጣና ተቃውሞ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በድርጊቱ የተሳተፉ እና በማህበራዊ ገጾች ላይ የለጠፉት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ከመዋላቸውም በተጨማሪ፤ የአምቦ ዩኒቨርሲቲም የዲሲፕሊን ቅጣት ለማስተላለፍ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ