የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዲስ የጸደቁ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደረጃዎች ላይ ከሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጥራት ቁጥጥር እየተደረገባቸው ከሚገኙ ምርቶች በተጨማሪነት አዲስ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ካውንስል የጸደቁ የተለያዩ ለሕንጻ አገልግሎት የሚውል መስታወት፣ የተለያዩ ለሕንጻ አገልግሎት የሚውሉ የአልሙኒየምና የአልሙኒየም ቅይጥ ምርቶች፣ የቀለም ምርቶች፣ የተሽከርካሪ መቀመጫ ቀበቶ፣ የሞተር ሳይክል ሄልሜት፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ዲቫይስ እና የተሽከርካሪ ኢንስፔክሽን ስታንዳርድ ቁጥጥር የሚደርግባቸው መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ምርቶች ከዚህ ቀደም ቁጥጥር እየተደረገባቸው ከሚገኙት አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ጋር በተጨማሪነት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ወይም ከሀገር እንዲወጣ ስለመፍቀድ ማረጋገጫ እየተሰጣቸው እንደሚስተናገዱ ተነግሯል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የባንክ ፍቃድ አግኝተው ወይም በፍራንኮ ቫሉታ ፍቃድ ግዥ ተፈጽሞባቸው በመንገድ ላይ ያሉትን ምርቶች በነበረው አሰራር ለማስተናገድ እንዲቻል የአራት ወራት የእፎይታ ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት የቁጥጥር ሥራዉ ከሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ማንኛውም እነዚህን ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ አስመጪ ምርቶቹን በኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ መስፈርትን አሟልቶ እንዲያስመጣ አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አዲስ የጸደቁ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደረጃዎች ላይ ከሰኔ ወር ጀምሮ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገለጸ
