ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤ፤ የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስተር መላኩ አለበል፤ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባሰሙት ሪፖርት፤ በግማሽ ዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 369 ሚሊየን 110 ሺሕ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

Post image

እንዲሁም በግማሽ ዓመቱ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን በላይ ግብዓት ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

"በሀገር ውስጥ ለአምራች ዘርፋ ግብዓት የሚሆኑ የኬሚካል ግብዓቶች፣ የካፒታል ዕቃዎች፣ ማሽነሪዎች እና መለዋወጫ የመሳሰሉትን በሙሉ አቅም በማምረት ረገድ እንደ ሀገር በቂ አቅም ባለመፈጠሩ ምክንያት በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ ሀገራት ገዝተን ማምጣት ስላለብን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታችን ከፍ እንዲል አድርጎታል" ሲሉም ተናግረዋል።

ሚንስትሩ አክለውም በመንግሥት የሚተዳደሩ የስኳር ፋብሪካዎች ችግር ውስጥ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ተስፋሁን ቦጋለ፤ የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ችግር ላይ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ለአብነትም የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ጠቅሰዋል፡፡

ፋብሪካው በዓመት 242 ቶን የማምረት አቅም ቢኖረውም፤ በገንዘብ እጥረት እና በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ሥራ ማቆሙን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ተቋሙ የ4 ወር ደመወዝ ለሠራተኞቹ መክፈል አለመቻሉ አስረድተዋል፡፡

የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም እንዲሰሩ እገዛ ለማድረግ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ አምራች ኢንዱስትሪውን በግማቆሙን ይሁን በኃይል አቅርቦት ሊደገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በአማራ ክልል በጃዊ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፤ በ2014 ዓ.ም የስኳር ማምረት ሥራውን መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ውሎ የህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም እጩ ዋና ዕምባ ጠባቂ፣ ምክትል ዕምባ ጠባቂ እና የዘርፍ እምባ ጠባቂ ሹመቶችን መርምሮ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ፣ የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ እና የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጆችን ያጸድቃል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ