ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሜሪካዋ ካፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ላይ አዲስና ከፍተኛ መጠን ያለው ሰደድ እሳት መቀስቀሱ ተገልጿል፡፡

በትናትናው ዕለት ለሊት ላይ የተቀሰቀሰውንና በፍጥነት በሚጓጓዝ ንፋስ ስርጭቱ እየተስፋፋ የሚገኘውን ይህን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር በርካታ ቁጥር ያላቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሌሊቱን ሲረባበቡ የቆዩ ሲሆን፤ ይህም እሳት ተጨማሪ ሞት እና ውድመት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።

ሰደድ እሳቱ እስካሁን ከ3 ሺሕ 800 ሄክታር በላይ መሬት ማካለሉ የተነገረ ሲሆን፤ እሳቱ መከሰቱን ተከትሎ 31 ሺሕ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

Post image

በተጨማሪም 23 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተጠንቀቅ እንዲዘጋጁ ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን፤ 500 ታራሚዎችም በአካባቢው ከሚገኝ ማረሚያ ቤት ወደ ሌላ ስፍራ መዘዋወራቸው ተነግሯል፡፡

ከሎስ አንጀለስ በስተሰሜን በሚገኘው ካስታይክ ሀይቅ አካባቢ በፍጥነት እየነደደ ያለውን እሳት ለመቆጣጠር እስካሁን፤ 4 ሺሕ በሚጠጉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በበርካታ የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላኖች ታግዘው ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በሰደድ እሳቱ እስካሁን የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት አለማድረሱ ተመላክቷል፡፡

Post image

ካስታይክ በበጋ ወራት ብዙ ጎብኚዎችን የሚስብ ሀይቅ ያላት ከተማ ስትሆን ወደ 19 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ አላት፡፡ ነገር ግን ወደ 224 ሺሕ ሰዎች ለሚኖሩባት የሳንታ ክላሪታ ከተማ እና ማጂክ ማውንቴን ፓርክ አቅራቢያ መገኘቷ እሳቱ እንዳይስፋፋ ስጋት ሆኗል።

የሎስ አንጀለስ ካውንቲ የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ አንቶኒ ማርሮን “ሁኔታው ተለዋዋጭ ነውና እሳቱ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ቢሆንም አሁንም የበላይነቱን እየወሰድን ነው” ማለታቸውን ዌል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

አሁንም ቢሆን ባለሥልጣናቱ ለአደገኛ የእሳት አደጋ ሁኔታዎች ማስጠንቀቂያ እስከ አርብ ማለዳ ድረስ በሥራ ላይ እንደሚውል የገለጹ ሲሆን፤ "የድርቅ ሁኔታዎች አካባቢውን ለአደጋ እንዲጋለጥ አድርጓል" ብለዋል።

Post image

በሌላ በኩል ከ16 ቀናት በፊት በሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢው ከተቀሰቀሰው እሳት ውስጥ ከባድ የተባሉት የኢቶንና ፓላሲደስ እሳቶች አሁን እየነደዱ መሆኑ ተገልጿል።

የኢቶን ሰደድ እሳት እስካሁን 5 ሺሕ 600 ሄክታር መሬት ማካለሉ የተገለጸ ሲሆን፤ ፓላሲደስ እሳት ደግሞ ከ9 ሺሕ 489 ሄክታር በላይ መሬት ማካለሉ ተመላክቷል።

አሁን ላይ የኢቶን እሳትን 91 በመቶው መቆጣጠር መቻሉ የተገለጸም ሲሆን፤ በሎስ አንጀለስ በስተ ምዕራብ 9 ሺሕ 489 ሄክታር ያወደመው ትልቁ ፓሊሳድስ እሳት 70 በመቶው መቆጣጠር ተችሏል ተብሏል፡፡

ይህ ከባድ የሰደድ እሳት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም 27 ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እንዲሁም እስካሁን ድረስ እነዚህ ሁለት እሳቶች ከ16 ሺሕ በላይ መኖሪያ ቤቶችን እና ሕንጻችን አውድመዋል፡፡

የካሊፎርኒያ የደን እና የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል፤ እ.ኤ.አ. በ2025 ብቻ 240 ሰደድ እሳቶች ተከስተው 40 ሺሕ 462 ሄክታር መሬት መቃጡን አስታውቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ