ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም. የ6 ወር አፈጻጸምን አስመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ 8 ሚሊዮን 874 ሺሕ ቶን የኢንዱስትሪ ግብአት ለማቅረብ ታቅዶ፤ 9 ሚሊዮን 527 ሺ 593 ቶን ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት፤ አቅርቦቱ በዋናነት በጨርቃ ጨርቅ፣ በምግና መጠጥ፣ በኬሚካል፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቴክኖሎጂና ኢንጅነሪግ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተቋማት የሚውል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዚህ ዓመቱ አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ42 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዚህም ባለፈው ዓመት 6 ሚሊዮን 7መቶ ሺሕ ቶን የነበረ ሲሆን፤ አሁን ካለው አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሚንስትሩ አክለውም፤ ይህ ውጤት የተመዘገበው ዘርፉን የሚያጠናክሩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስፋፈትን ተከትሎ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ የሚያስችሉ ወጣቶችን ወደ ዘርፉ እንድቀላቀሉ በማድረግ እንዲሁም የማምረት አቅምን በማጎልበት የመጣ ውጤት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአጠቃላይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 62 ነጥብ 4 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ፤ 61 ነጥብ 2 በመቶ በማድረስ የእቅዱን አፈፃጸም 98 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የማምረት አጠቃቀም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 56 ነጥብ 04 ጋር ሲነፃፀር የ9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የገለጹት አቶ መላኩ፤ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ከተደረሰበት 59 ነጥብ 06 አንፃር የ3 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
አክለውም ኢንዱስትሪ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ሚና ያለው ዘርፍ በመሆኑ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በማጠናከር ለሌሎች ዘርፎች እድገትና መነቃቃትንም የፈጥራል ብለዋል፡፡
ይህ አፈጻጸም የኢንዱስትሪውን አቅም የበለጠ የሚያጎለብት ሥራ በመሆኑ ተጠናክረው የሚሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 9 ሚሊዮን 5 መቶ 27 ሺሕ ቶን የኢንዱስትሪ ግብአቶች ማቅረቡን ገለጸ
የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም 61 ነጥብ 2 በመቶ መድረስ መቻሉ ተነግሯል