ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ለ2ተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቁርዓን እና የአዛን ውድድር ሽልማት ከ60 ሀገራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎችና የልዑካን ቡድን ተሳታፊዎች እንዲሁም ኢንቨስተሮችና ታዋቂ ግለሰቦች ይገኙበታል ተብሏል።
በዘይድ እብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር አዘጋጅነትና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠባቂነት እንደሚካሄድ ማህበሩ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።
ውድድሩ በሁለት መርሀ ግብር መከፈሉ የተለገጸ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ጥር 21 ቀን 2017 በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ይካሄዳል ተብሏል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ሴቶች ተሳታፊ እንዳልነበሩ የተገለጸ ሲሆን በዘንድሮው የቁርዓን ውድድር ተሳታፊዎች፣ ዳኞች እና ተጋባዥ እንግዶች ይሆናሉ ተብሏል።
ሁለተኛውና የፍጻሜው ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የሐይማኖት አባቶች የእስልምና እምነት ተከታዮች ጨምሮ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ለዚህም ውድድር የፊታችን ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ከ 60 ሀገራት 100 ተወዳዳሪዎች እንዲሁም 11 ዳኞች ከሁሉም አህጉር ኢትዮጵያ እንደሚገቡም ተመላክቷል፡፡
የውድድሩ የመግቢያ ትኬቶች የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ በአዋሽ ባንክ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ፣ በሂጅራ ባንክ፣ በዳሽን ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎች እና በቴሌብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡
ይህ የዓለም አቀፍ የቁርዓን እና አዛን ውድድር ሽልማት ፕሮግራም የሀገር ባህልን፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንትን ከመሳብና ከማስተዋወቅ አንፃር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተነስቷል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ከ50 እስከ 60 ሺሕ የሚሆኑ ታዳሚዎች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ውድድር 56 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን፤ ፖርቶን፣ የመን እና ሱዳን አሸናፊ እንደነበሩ ይታወቃል።
በዘንድሮው ውድድርም ሦስት ኢትዮጽያዊያን እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የድርሻውን እንደሚወጣ ተገለጸ
![የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የድርሻውን እንደሚወጣ ተገለጸ](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2F0809875bedcc07ba44fe769d08297248798a4f8b-1280x549.jpg&w=1280&h=549&f=webp)