ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ሀገራት የተሞከረባትን ወረራ መቋቋሟ የቀደመውን ሀገራዊ መግባባት እንደሚያሳይ በትናንትናው ዕለት ጥር 14 ቀን 2017 በተካሄደው ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች ፎረም ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

ውይይቱ "ብሔራዊ መግባባት" በሚል ርዕስ ሲካሄድ 'የብሔራዊ መግባባት ታሪካዊ መሰረቶች' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ አብዲዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር)፤ "በቀደመው ጊዜ የውጭ ሀገራት ወረራዎችን ኢትዮጵያ መቋቋም መቻሉ የነበራትን የሀገራዊ ተግባቦት ማሳያ ነው" ብለዋል።

Post image

"ጠንካራ ሀገርን ለመመስረት የጋራ ማንነት እና የጋራ መግባባት ያስፈልጋል" ያሉ ሲሆን፤ "ይህ መሆን ካልቻለ ሀገር ጠንካራ ሆና መቀጠል አትችልም" ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም የጋራ ማንነት ለሀገር ህልውና መሰረታዊ ነው በማለት፤ ይህን ለማድረግ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያያላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችም ለብሔራዊ መግባባት መሰረቶች መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ የነበሩ ጥንካሬዎችን የበለጠ ማስቀጠልና ያልተዳሰሱትን ማካተት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ "የብሔራዊ መግባባት ታሪካዊ መሰረቶች በኢትዮጵያ፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ የብሔራዊ መግባባት ተግዳሮቶች ምንድናቸው? እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት በመጪዋ ኢትዮጵያ እታፈንታ ላይ ምን ይዞ ይመጣል?" የሚሉ ሦስት አበይት ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በዚህም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ መግባባት መመጣት ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን በ10 ክልሎችና በ2 ከተማ አስተዳደሮች መደረጉ ተገልጿል።

Post image

እንዲሁም ኮሚሽኑ 11 ክልል ላይ የምክክር ሥራውን መጀመሩም ተጠቁሟል።

በውይይት መድረኩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌንን ጨምሮ በርካታ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ