ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የተጠረጠሩ በርካታ ደላሎች ተከሳሽና ምስክር ባለመቅረባቸው በርካታ መዝገቦች እየተቋረጡ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የተደራጁ ወንጀሎችና ድምበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል እዮሲያስ አበጀ፤ በኢትዮጵያ በየአካባቢው ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ እና ድንበር ሲያሻግሩ የሚያዙ ግለሰቦች ቁጥር በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል።
ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹን በሕግ ለመጠየቅ ምስክሮች በመጥፋታቸው፣ መረጃ በማጣት እርምጃ በመውሰድ ሂደት ላይ ክፍተት በመፍጠሩ ክሳቸው ተቋርጦ ነጻ እየተለቀቁ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።
"ተጠርጣሪዎች ለምስክሮች መደለያ በርካታ ገንዘብ በመስጠት፣ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ በማድረግ እንዳይመሰክሩ አድርገዋል" ሲሉም አብራርተዋል።
"የወንጀሉን ተሳታፊዎች ተጠያቂ ለማድረግ ፖሊስ፣ ዐቃቢ ሕግ እና ዳኛ ብቻውን መከላከል አይችልም" ያሉት ኢዮሲያድ፤ ህብረተሰቡ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎችን ጠቃሚ አድርጎ ማሰቡም ለፍትህ መጓደሉ አንዱ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።
"ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ውስብሰብ በመሆኑ፤ ዜጎች ለሞት ና ለከፋ ችግር እያጋለጠ የሀገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል" ሲሉም አክለዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በብዛት በሕገወጥ መንገድ እየተሰደዱ እና አብዛኛዎቹ ያሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ ሕይወታቸው መንገድ ላይ የሚያልፍበት እና ለእስር የሚዳረጉበት ሁኔታም ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በየአካባቢው ከሴቶች ይልቅ የሚሰደዱ ወንዶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የችግሩን ግዝፈት በመረዳት ሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው የመከላከል ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ በኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ