ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ በግል እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ በሚገኙ ከ300 በሚበልጡ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ "የንግድ ተቋማቱ እርምጃ የተወሰደባቸው የመማር ማስተማር ሂደቱን በሚያውክ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው" ብሏል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለአሐዱ እንደተናሩት፤ እርምጃ ከተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት መካከል፤ ጭፈራ ቤቶች፣ የመኝታ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ቁማር ቤቶች እና መሰል ተቋማት ይገኙበታል፡፡

በዚህም በተቋማቱ ላይ የማሸግ፣ የንግድ ፍቃድ መሰረዝ እንዲሁም የገንዘብ መዋጮን ጨምሮ ሌሎች ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ "በተመሳሳይ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ከትምህርት ተቋማት ከ500 ሜትር በላይ መራቅ ይገባቸው ነበር" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ባለመሆኑም ምክንያት ተማሪዎች ለአጉል ልማዶች እንዲዳረጉ ከማድረጉም በተጨማሪ በትምህት ውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ይህንን ሥራ ሲያከናውን ከሕብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ከትምህርት ቢሮ እና ከሰላምና ፀጥታ ጋር በመተባበር እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአጠቃላይ በአዲስ አበባ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ተግባራት በሚፈጽሙ 3 ሺሕ 486 አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ሻለቃ ዘሪሁን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በ6 ወር የሥራ አፈፃፀም ከ27 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት 1 መቶ 34 ሺሕ 98 የደንብ ተላላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገለጹት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፤ ከነዚህ የደንብ ተላላፊዎች 1 መቶ 35 ሚሊየን የሚገመት ብር ከቅጣት መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

አክለውም የተገኝውን ገንዘብ ለመንግሥት በፋይናንስ አሰራር መሰረት ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ