መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሕገ-ወጥ የእንሰሳት አደን ምክንያት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት የዋልያዎች ቁጥር ከ1 ሺሕ ወደ 306 መቀነሱን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጽያ በተለይም በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ብርቅዬ የዋልያዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ መቀነሱን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መኮንን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ለብርቅዬ ዋልያዎቹ ቁጥር መቀነስ ዋና ምክንያቱ የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም፤ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሕገ-ወጥ የእንስሳት አደን መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም የዋልያዎቹ ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው አሃዛዊ ቁጥር አንፃር ሲታይ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው አሳሳቢ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን የዋልያ ዝርያ አሃዛዊ ቁጥር መቀነስ በተመለከተ ቁጥራቸውን ወደ ነበረበት ለመመለስ ያለመ የውይይት መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ መካሄዱን ጠቁመዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም "ለዋልያዎቹ መመናመን እንደ ምክንያት የሚጠቀሰውን ሕገ-ወጥ አደንን በተመለከተ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በሰሜን ተራሮች አካባቢ የሚገኘው አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንደሽን /African wild life foundation/ ጋር በመሆን ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከዞን አመራሮች ጋር ሰፊ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
በተለይ የፌዴራል እና የክልል ኮሚቴ ተዋቅሮ በሰሜን ተራሮች እና በባሌ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ በትኩረት ለመሥራትና የተገኝውን ዉጤት ከአንድ ወር በኋላ ግምገማ እንደሚደረግም አቶ ሰሎሞን ለአሐዱ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሕገ-ወጥ የእንሰሳት አደን ምክንያት የዋልያዎች ቁጥር ከ1 ሺሕ ወደ 306 መቀነሱ ተገለጸ
