መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት በተያዘው የመጋቢት ወር ላይ ከሶማሊያ ጋር በምታደርገው ቴክኒካዊ ድርድር መግባባት ላይ ከተደረሰ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ፤ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር በካቲት ወር ላይ መደረጉ ይታወቃል።

በመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር ልዑካኑ የአንካራ ቃል ኪዳንን ራዕይ እውን እንዲሆን ለማድረግ እና ለሁለቱ ሀገራት ጠቃሚ ለሆነ ዘላቂ ልማት መሠረት ለመጣል "ተጨባጭ" ሥራ ማከናወን እንደሚጀምሩ በማንሳት፤ ሁለተኛው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር በተያዘው መጋቢት ወር እንደሚደረግ ተገልጿል።

አሐዱም "በሁለተኛው ዙር ድርድር ከኢትዮጵያ ምን ይጠበቃል? ድርድሩስ ምን ውጤት ይዞ ሊመጣ ይችላል" ሲል ጠይቋል፡፡

"የቴክኒካዊ ድርድር ማጠንጠኛ ስርዓቱ (ፍሬም ወርክ) በአንካራው ስምምነት የተቀመጠ ነው" ያሉት የቀድሞ ዲፕሎማት ደያሞ ዳሌ፤ ኢትዮጵያ ወደብ ከማግኘት ጋር ተያይዞ ወጪዎችና የደህንነት ጉዳይ ላይ ማተኮር እንዳለባት ገልጸዋል።

እንዲሁም የወደብ አጠቃቀም ሕጎች እና የኢንቨስተመንት መንገድን በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል የሚነሳ መሆኑን ገልጸው፤ ከድርድሩ ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቁ አንስተዋል።

ሌላኛዉ አሐዱ ያነጋገራቸው የቀድሞው ዲፕሎማት ዶ/ር ተሻለ ሰብሮ፤ ድርድሩ እዚህ ደረጃ መድረሱን አድንቀው ከዚህኛው ድርድር ጥሩ ውጤት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

'ኢትዮጵያ የትኛውን ወደብ ታገኛለች?' 'በምን ያህል ስፋት?' 'ለምን አገልግሎት የሚውል?' የሚለውም፤ በቴክኒካዊ ድርድሩ ላይ መነሳት ያባለባቸው ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

"አሁን ላይ የባህር በር ማግኘት ለገቢና ወጪ ንግድን አላማው ያደረገ ቢሆንም፤ የባህር ሃይል ቤዝ ማቋቋሚያ ስፍራም ተነጣጥሎ የማይታይ ነው" ብለዋል።

በአንፃሩ "ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በምታደርገው ጥረት መነሻ በማድረግ በጦርነት ወደብ ለማግኘት እንደምትፈልግ አድርጎ የማሳየት ነገር አግባብ አይደለም" ሲሉም አሐዱ ያነጋገራቸው የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤት አባላት ጋር በነበራቸው ስብሰባ "የቀይ ባህር ፍላጎታችን ከሶማሊያም፣ ከጀቡቲም፣ ከኬንያም የሚያጣላን አይደለም፡፡ የተገደበም አይደለም፡፡ የሚመለሰው ግን በውይይት መሆን አለበት" ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እንዲሁም ከሰሞኑ ከኤርትራ ጋር ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት እየተንጸባረቀ መሆኑን አስታውሰው፤ "መንግሥት ለቀይ ባህር ሲል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የለውም፡፡ ፍላጎታችን መነጋገር ነው" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ስለማመናቸው አብራርተዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ