ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያዊያን በሕገ-ወጥ ደላሎች 'ወደ ተለያዩ ውጭ ሀገራት እንልካችኋለን' በሚል በተሳሳተ መረጃ ወደ ከፋ ችግር እየገቡ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በርካታ ዜጎችም በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታልለው እና ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ከሀገራቸው እየወጡ፤ ለከፍተኛ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ዜጎች በሕገ-ወጥ ደላሎች ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚሄዱ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም በርካቶችን ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክቷል።

ይሁን እንጂ በተለያየ ሁኔታ ወጣቶችና ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ለአካላዊ ጥቃት፣ ለረሀብ፣ ለአይምሮ በሽተኛነት እንዲሁም ለተለያ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ሴቶች እንደሚደፈሩና ከዚህም አልፎ ሕይወታቸዉን እስከማጣት ድረስ ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ዜጎች በሕገ ወጥ ደላሎች በመታለል ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ ማንኛዉም ማህበረሰብ ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሕገወጥ ደላሎችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ከሚመለከተዉ አካል ጋር በጋራ በመሆን ቁጥጥር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2012 ዓ.ም በሰው መነገድና ሰውን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 እንዲወጣ ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።