ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፉት ስድስት ወራት የሕግ ተገዢነትን ለማስፈን በተደረገው ጥረት 1 ሺሕ 165 ሃሰተኛ ደረሰኝ ጥቅም ላይ እንዳይውል መደረጉን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡

ደረሰኞቹ በ153 ድርጅቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበር ሲሆን፤ በዚሁም 1 ቢሊዮን 210 ሚሊዮን 91 ሺሕ 184 ብር ሃሰተኛ ግብይት ለታክስ ዓላማ እንዳይውሉ መደረጉም ተመላክቷል፡፡

"የሕግ ተገዢነትን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ እንዲህ ባለ አላስፈላጊ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አካላትም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ እንዲሁም ከጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ ከ451 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ውስጥ ታክስ 254 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 247 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም፤ ከውጭ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ 190 ነጥብ 9 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ 203 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰንሰቡን ተናግረዋል፡፡

በድምሩ ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ 451 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 101 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን አንስተዋል፡፡

የገቢ አሰባሰቡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ106 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም የ110 በመቶ ብልጫ እንዳለውም መናገራቸውን አሐዱ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡