ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የ2017 የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ (የ12ኛ ክፍል) ፈተና ምዝገባ ነገ ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል።

በተለያየ ምክንያት ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ካሉ ዛሬ እና ነገ እንዲመዘገቡ ጥሪ ያቀረበው አገልግሎቱ፤ ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ፈተናውን እንደማይፈተኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መልዕክት አሳስቧል።

የተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ ከታሕሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦንላይን እየተከናወነ ሲሆን፤ እስካሁን 499 ሺሕ 200 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ለመውሰድ መመዝገባቸውን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

እንዲሁም በአጠቃላይ በመደበኛ እና በግል 750 ሺሕ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በመደበኛው ፕሮግራም 600 ሺሕ ተማሪዎች ለመመዝገብ ዕቅድ መያዙም የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን 82 በመቶ የሚሆኑ መደበኛ ተማሪዎች መመዝገባቸው ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም በግል የሚፈተኑ 150 ሺሕ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ እስካሁን 1 ሺሕ 100 ተማሪዎች ብቻ ምዝገባ ማድረጋቸውን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ከተፈተኑ 684 ሺሕ 205 ተማሪዎች መካከል፤ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት 5 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡