የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚያቀርበው የስራ ስምሪት ተጠቃሚ ለመሆን ክልሎች ላይ በማሰልጠኛ ተቋማት በኩል ሰልጥነው፤ ወደተለያዩ አረብ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች የኦንላይን ምዝገባቸው እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ጉቦ እየተጠየቁ ለተጨማሪ ወጭ መዳረጋቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ለ21 ቀናት የሚሰጠውን ስልጠና ጨርሰው ፈተናም አጠናቅቀው የመጨረሻ ምዝገባቸው በኦንላይን ካልተከናወነ ቲኬት እንደማይቆረጥላቸውና ቪዛ ካወጡም ቀነ ገደብ እንደሚያልፍ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ስልጠናቸውን አጠናቀው፣ የሙያ ብቃት ምዘና (COC) ፈተናውንም አልፈው ሰርተፊኬት ጭምር ተሰጥቷቸው እያለ ነገር ግን ኦንላይን ምዝገባው እንደማይከናወንላቸው ገልጸዋል።

ለአገልግሎቱ ከሚከፈል መደበኛ ክፍያ በተጨማሪ አሰልጣኝ ተቋማት በኩል 'በፍጥነት ኦንላይን እንዲሆንላችሁ ከ5 ሺሕ እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ገንዘብ ክፈሉ' ስለመባላቸው ለአሐዱ አስታውቀዋል።
ጉዳዩን በማሰልጠኛ ተቋማት በሚገኙ ቅርንጫፎች እየሄዱ ቢጠይቁም፤ 'ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው ሲስተሙን የያዘው ጠብቁ' እየተባሉ ብዙ ጊዜ በማለፉ በተለይም አብዛኞቹ ሴቶች በመሆናቸው እየተቸገሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በተለይም ከክፍለ ሀገር የሚመጡ ዜጎች ለብዙ እንግልት ከመዳረጋቸውም በላይ፤ የቪዛ ቀነ ገደብ በማለፉ የተቃጠለባቸው መኖራቸውንም አክለው ገልጸዋል።
አሐዱም የተገልጋዮችን ቅሬታ ተቀብሎ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን አነጋግሯል።
ለውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ለ21 ቀናት የሚቆይ ስልጠና በቤት ሙያ ውስጥ ለተሰማሩ ዜጎች እየተሰጠ ምዘናቸው ተከናውኖ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዘረጋው የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት (LMIS) መሰረት፤ በመጀመሪያ በስልጠና ተቋማት በኩል መረጃው እንደሚላክ በሚኒስቴሩ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት((IMIS) ፕሮጀክት ፅ/ቤት ኃላፊ ብርሀኑ አለቃ ለአሐዱ ገልጸዋል።
በማስከተልም መረጃው ወደ ምዘና ተቋማት እንዲሁም ወደ ስራና ክህሎት እና ወደ ኤምባሲ የሚሄድበት አካሄድ መኖሩን ጠቁዋል፡፡
በመሆኑም ስልጠናው የሚሰጠው ሙሉ ለሙሉ በክልል ደረጃ ሲሆን፤ ክልሎች ራሳቸው ብቁ የሆኑ የስልጠና ተቋማትን መርጠው 'የኦንላይን ሲስተም ውስጥ እንዲገቡ ይፈቀድ' ብለው ለስራና ክህሎት ደብዳቤ ፅፈው ወደ ሲስተም እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ለምዘና ተቋማትም ብቃታቸው ተረጋግጦ በደብዳቤ የሚጸድቅበት አካሄድ መኖሩንም ኃላፊው አብራርተዋል።
በዚህ ሂደት ግን መረጃው ክልሎች በሚልኩት መረጃ መሰረት የሚገኝ በመሆኑ፤ የትኛው ክልል ምን ያክል ሰው አሰልጥኖና ፈትኖ ውጤቱንም በወረቀት አስረክቦ ወደ ኦንላይን ሲስተም የማስገባቱን ሥራ እንዳላከናወነ የሚገልፅ መረጃና በዚህ ጉዳይ የተቸገረ ሰው ስለመኖሩ ግን እውቅናው እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ክፍያን በተመለከተም በክልሎች የሚወሰን ቢሆንም፤ ነገር ግን አሁን ባለው አሰራር በፌዴራል ደረጃ ለስልጠና ተቋማት አንድ ሰው ከ1 ሺሕ 500 ብር በላይ መክፈል እንደሌለበት መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
አክለውም ለውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ከፓስፖርትና ጤና ምርመራ ውጪ የሚከፈል ምንም አይነት ገንዘብ እንደሌለ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኃላፊው "የኦንላይን ሲስተሙ ምዝገባ የሚጠናቀቀው ክልሎች በሚልኩት መረጃ መሰረት በመሆኑ፤ ጉዳዩን በቀጥታ ስራና ክህሎት ገብቶ የሚፈታው ባይሆንም እንኳ ክልሎች ጋር በመነጋገር በአስቸኳይ እነዚህን ሰዎች እንዲስተናግዱ እንነጋገራለን" ሲሉም ምላሽ ሰተዋል፡፡
ሆኖም ግን በዚህ አሰራር ቅር የተሰኙና ከተመደበው ገንዘብ ውጪ እንዲከፍሉ የተደረጉ ካሉ ማስረጃቸውን በመያዝ በማንኛውም ሰዓት ወደ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር በመሄድ ጥቆማ ቢሰጡ ገንዘባቸው እስከነካሳው እንዲመለስ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በጥቆማው መሰረት ይህንን ሥራ በፈፀሙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ