መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ስርዓቱ ፍትሀዊነት ሲያዛቡ እና ከተማዋ ከንግዱ እንቅስቃሴ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ሲያሳጡ የነበሩ 742 ሕገ-ወጥ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት በክፍለ ከተማው በመንደር የንግድ ቁጥጥር አሰራር ስርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016 መሠረት፤ በ11ዱ ወረዳዎች ላይ የቁጥጥር ባለሙያዎች በማደራጀት በንግድ ድርጅቶች ላይ የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መስራቱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ፍቅሬ አስታውቀዋል፡፡

በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች የንግድ ስርዓቱ ፍትሀዊነት ሲያዛቡ እና ከተማዋ ከንግዱ እንቅስቃሴ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ሲያሳጡ የነበሩ 742 ሕገ-ወጥ የንግድ ድርጅቶችን የመለየት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

Post image

ከእነዚህም ውስጥ፤ "ያለ ንግድ ፈቃድ 279፣ ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ 153፣ ያለ ደረሰኝ ግብይት 3፣ ከአድራሻ ውጭ 57፣ ከዘርፍ ውጭ 138፣ ሌሎች 112 ተለይቷል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ አሸናፊ አያይዘውም ከእነዚህም ውስጥ 370 የማሸግ እና 62 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ መሰራቱን የገለጹ ሲሆን፤ 148 ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ወደ ከተማ የመላክ ሥራ መሰራቱን እና ቀሪዎቹም እንዲያስተካክሉ የጊዜ ገደብ መሰጠቱን አንስተዋል፡፡

Post image

አክለውም በብሎክ ደረጃ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች እንዲሰሩ የተመደቡ ባለሞያዎች ሥራውን በአግባቡ ባለማከናወናቸው በቀጣይ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹ ሲሆን፤ የንግዱም ማህበረሰብም ሕጋዊ የንግድ ስርዓቱን ተከትሎ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ