መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ሰሚት ለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ በቡድን በመሆን የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ከነ ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

በአካባቢው ላይ አሽከርካሪዎች ልምምድ የሚያደርጉበትና የተለያዩ ግለሰቦች የሚዝናኑበት መሆኑን ሲያጤኑ የቆዩት ተከሳሾቹ፤ በሽጉጥ በማስፈራራት፣ ጉዳት በማድረስና የያዙትን ንብረት በመቀማት ከአካባቢው ሲሰወሩ መቆየታቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

Post image

ግለሰቦቹ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች መፈጸማቸው ሪፖርት የደረሰው የአራብሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም ባደረገው ክትትል፤ አራት ተጠርጣሪዎችን ለወንጀል መፈፀሚያ ከሚጠቀሙበት ሽጉጥ ጋር በቁጥጥር ማዋሉ ተገልጿል፡፡

Post image

በተጨማሪም የተሰረቁ ንብረቶችን፣ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ3 5616 አ/አ በሆነ ሞተር ሳይክል እንዲሁም፤ እየተንቀሳቀሱ የሚቀበሉ ተጨማሪ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የምርመራ መዝገብ በማደራጀት በዐቃቤ ሕግ በኩም ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉም ተመላክቷል፡፡

የተከሳሾቹ የክስ መዝገብ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚኩራ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ እየታየ ሲሆን፤ በማረሚያ ቤት ሆነውም ጉዳያቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን ሲፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ቆመው ሲመለከቱ እንደነበረ ያስታወሰው ፖሊስ፤ ሕብረተሰቡ ወንጀል እየተፈጸመ እያየ ለፖሊስ መረጃ አለመስጠቱ ወይም እየተፈጸመ ያለን ወንጀል እንዲቋረጥ አለማድረግ በህግ ተጠያቂ ሊያርገው እንደሚችል በመገንዘብ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ