መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገሪቱ ቤት ለቤት እየዞሩ በእጅ ገንዘብ የመሰብሰብ የሚሰጠውን የአገልግሎት ሂደት በማዘመን በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት አስታውቋል።

የጤና መድኅን ስርዓቱ በኢትዮጵያ ከተጀመረ 13 ዓመታትን ማስቆጠሩን ያነሱት በአገልግሎቱ የአባላት አስተዳደርና ሃብት አሰባሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ጉደታ አበበ፤ በተለይም በ2004 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው አዋጅ መሠረት በ13 ወረዳዎችና አራት ክልሎች ላይ በሙከራ ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም የጤና መድህን ስርዓቱን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ በማንሳት፤ ከዛም ውስጥ የገንዘብ አሰባሰብ ስርዓቱን የማዘመንና ወደ ዲጂታል ሲስተም የመቀየር ሥራን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በሰፊው እየተሰራበት እንደሚገኝ ለአሐዱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ተደራሽ እንዲሆንና የአባላት መረጃን እንዲይዝ ተደርጎ ከሚሰራበት የዲጂታል ገንዘብ አሰባሰብ ስርዓቱ በተጨማሪ፤ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡንም ዘመናዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም ጥራት ያለውን የሕክምና አገልግሎት ለዜጎች ከማድረስ አንፃር በርካታ የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን በመmጥቀስ፤ አሁንም ግን የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

ማንኛውም ዜጋ በዓመት አንድ ጊዜ የሚጠበቅበትን ክፍያ ብቻ እስከ ከፈለ ድረስ ተጨማሪና ድንገተኛ የሆነ ወጪን በማውጣት መታከም እንደማይገባው የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ ከሕክምና ተቋማቱ በተጨማሪ በተለይም ከቀይመስቀል፣ ከነማ እና የማህበረሰብ ፋርማሲዎች ላይ መድኃኒት የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም ዜጎች የጤና መድኅንን በመጠቀም የተሳለጠ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻልና የመድኃኒት እጥረቱን ለመቅረፍ፤ በቀጣይ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ተጠናክሮ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ