መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ፤ ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ መድኃኒቶችን በቀመሙና በሸጡ የመድኃኒት መደብሮች ላይ ሕጋዊ እርምጃዎች መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር ገልገሎ ኦልጅራ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ 'በልዩ ሁኔታ ያለ ትዕዛዝ እንዳይሸጡ' በጥብቅ የተከለከሉ መድኃኒቶችን በራሳቸው ፍቃድ በሸጡ እና በቀመሙ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃው ተወስዷል።
ተቋማቱ የግለሰቦችን ፍቃድ ብቻ በመቀበል አገልግሎት በመስጠታቸው፣ መድኃኒቶችን በመቀመማቸውና በመሸጣቸውም እርምጃው እንደተወሰደባቸውም ተናግረዋል።

በድንገተኛ ፍተሻ ወቅት በተገኙት እነዚህ የንግድ መደብሮች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ያብራሩት የቁጥጥር ዳይሬክተሩ፤ 56ቱ ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም 38 ላይ ደግሞ የሥራ ፍቃድ ስረዛ እርምጃ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕገ-ወጥ ተግባራቱ እየተለመዱ መምጣታቸውን በማንሳትም፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሕገ-ወጥ ተግባራቱን መንሰራፋት በመመልከት በቂ የቁጥጥር ባለሙያዎችን በማሰማራት ችግሮችን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሕበረሰቡ ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ የሚሰጡ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳታቸው የከፋ በመሆኑ ከመሰል ድርጊቶች መቆጠብ እንዳለበት ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ፤ ባለሙያዎችም የሙያ ሥነ-ምግባራቸውን ተግባራዊ እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ