ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከነገ ጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ ጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በዚህም ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በ11ዱም ክ/ከተሞች ጥምቀተ ባህር ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ በ500 ሜትር ክልል ውስጥ ታቦታት ሲወጡና ሲገቡ እንዲሁም በሚሄዱባቸው መንገዶች ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረዥም ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
እንዲሁም ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ በጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር፦
👉 ከ6 ኪሎ አደባባይ - ምኒልክ ሆስፒታል
👉 ከምኒልክ ሆስፒታል - መከላከያ 3ኛ ሻለቃ አደባባይ
👉 ከ3ኛ ሻለቃ አደባባይ - 6 ኪሎ አደባባይ እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ
👉 ከዋልያ ቢራ - ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
👉 ከአቃቂ ዋናው መንገድ - ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
👉 ከ08 - አቃቂ ድልድይ ድረስ ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ መንገዱ ለተሽከርካሪዎች ዝግ ስለሚሆን አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ