ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም፤ በቂ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን የክልሉ ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

ጎጂ ባህላዊ ልማዶች እና ሃይማኖታዊ የሚመስሉ አካሄዶች የችግሩ ዋነኛ መንስኤ እንደሆኑ በቢሮው የሴቶችና ሕፃናት ተሳትፎ ንቅናቄ ዳይሬክተር ፋጡማ ሀንፈሬ ተናግረዋል።

ኃላፊዋ አክለውም የሴት ልጅ ግርዛት ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚያያዝ እንደሆነና ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎች ቢወሰዱም ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልጸዋል። በዚህም የማሕበረሰቡ የአመለካከት ችግር ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አንስተዋል።

የድርጊቱ ፈፃሚዎች ጎጂ ባሕሉን የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት ሥራቸው አድርገው ማከወናቸው ሌላኛው ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሯ የተቀመጡ ሕጎች የሦስት ወር እስርና የ500 መቶ ብር መቀጮ ቢኖርም፤ ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ክፍተት እንዳለበት አብራርተዋል። "በዚህ ጎጂ ልማድም ሴቶች ለጤና እክል እየተጋለጡ ይገኛሉ" ሲሉም የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

አያይዘውም "ችግሩ በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች፣ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ሴቶች መካከል ወደ 47 በመቶ የሚሆኑት ግርዛት ይፈፀምባቸዋል" ብለዋል።

በመሆኑም፣ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ኅብረተሰቡን ማስተማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አሳስበዋል።

በወልደሐዋርያት ዘነበ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ