ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሶ ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "ጎንደር ሦስት ነገሮች ተሸምነው የሠሯት ከተማ ናት።" ያሉ ሲሆን፤ እነሱም እምነት፣ መንግሥት እና ኅብረ ብሔራዊነት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Post image

"ነገሥታቱ ሥርዓተ መንግሥትና አብያተ መንግሥት አቁመዋል። የእምነት መሪዎች አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን ተክለዋል። እነዚህን ሁለቱን ፍለጋ ከመላ ኢትዮጵያና ከውጭ የመጡ ሰዎች ደግሞ ጎንደርን ኅብረ ብሔራዊት ከተማ አድርገዋታል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ጥምቀት በዓል ጎንደር የመንግሥት፣ የቤተ እምነትና የኅብረ ብሔራዊነት ማዕከል በመሆኗ ካቆየቻቸው ዕሴቶቿ አንዱ መሆኑንም አመላክተዋል።

አክለውም፤ "ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ አንዳንድ ነገር በአንዳንድ ቦታ ይደምቃል" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጎንደር የሚያከብር ሰው ለጎንደር ትንሣኤ ምስክር ነው" ብለዋል፡፡

Post image


"ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሷል፣ ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷል፣ ከተማው እንደ ሙሽራ እያበበ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

"በእውነቱ እነ ዐፄ ፋሲል፣ እነ ዐፄ ቴዎድሮስ ቢመጡ በአድናቆት ከተማቸውን መልሰው መጎብኘታቸው አይቀሬ ነው" ያሉም ሲሆን፤ የጎንደር ማንሠራራት የኢትዮጵያ ማንሠራራት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

Post image

በ17ኛው ክፍለ ዘመን በዓፄ ፋሲለደስ የተገነባው የፋሲል ግንብ የግቢው አጥር 900 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ በውስጡ 70000 ስኩየር ሜትር የመሬት ይዞታ ያካልላል።

የፋሲል ግንብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአውሮፓውያኑ 1979 የተመዘገበ የዓለም ቅርስ መሆኑ ይታወቃል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ