ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት 6 ወር ውስጥ ከ78 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶች የመንጋጋ ቆልፍ በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠቱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

አስከፊ የጤና ጉዳት የሚያደርሰው የመንጋጋ ቆልፍ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ለሕጻናት እንደሚሰጥ ሁሉ ነፍሰጡር ለሆኑ እናቶችም የሚወለደውን ልጅና እራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል ሲባል ክትባቱ እንደሚሰጥ በቢሮው የክትባት አገልግሎት አስተባባሪ ሙሉቀን ተስፋዬ ለአሐዱ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በ6 ወር ውስጥ ከ80 ሺሕ በላይ ነፍሰጡር እናቶችን ለመከተብ ታቅዶ 78 ሺሕ 758 የሚሆኑትን መከተብ መቻሉን ተናግረዋል።

የመንጋጋ ቆልፍ ክትባት ነፍሰጡር ላልሆኑትም እንደሚሰጥ የገለጹት የክትባት አገልግሎት አስተባባሪው፥ በዋናነት ለነፍሰጡር እናቶች የሚሰጥበት ምክንያት ሕጻናት ገና እንደተወለዱ በጨቅላነታቸው የሚከሰተውንና እናቶች ደግሞ ከወለዱ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የሚፈጠረውን የመንጋጋ ቆልፍ በሽታ ለመከላከል እንደሆነ ገልጸዋል።

ክትባቱ 5 ደረጃዎች እንዳሉት በመግለፅም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚፈጠረው እርግዝና ከበሽታው ለመጠበቅ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክትባቶች በቂ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ቀጥለው ለሚወለዱ ልጆች የሚያስፈልጉ እንደሆነም አብራርተዋል።

በከተማዋ ነፍሰጡር እናቶች ክትባቱን ለመውሰድ ያላቸው ግንዛቤ ጥሩ የሚባል ደረጃ እንደሚገኝ ገልጸው በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱ ያሳለፉ እናቶች ካሉ ወዲያውኑ መከተብ እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ