ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፤ ከዚህ ቀደም ወደ ሲስትም ያልገቡ 14 ገደማ ወረዳዎች እንደነበሩ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በእነዚህ በሦስት ክፍለ ከተሞች የነበሩ 14 ወረዳዎች በሙሉ ወደ ሲስተም እንዲገቡ በማድረግ ሙሉ በሙሉ የወረቀት መታወቂያ መስጠት መቆሙን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ "ከተማይቱ የማታቃቸው ከተለያዩ አካባቢዎች የወረቀት መታወቂያ ይዘው የመጡ አዲስ ነዋሪዎች ለመመዝገብ በታቀደው መሠረት በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል" ብለዋል፡፡

በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ 340 ሺሕ ዜጎችን በዚህ መንገድ መመዝገብ መቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ "ከተማይቱ የማያቃቸውን ነዋሪዎች ወደ ዲጂታል ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አንድ ዜጋ በነዋሪነት ከተመዘገበ በኃላ በርካታ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይም የነዋሪነት መታወቂያ ማውጣት፣ ያገባ እና ያላገባና የመሳሰሉት አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላል ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር የነዋሪነት ማረጋጫ የማግኘት አግልግሎት የማግኘት መብት እንዳለውም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡

"ከዚህም በዘለለ ኤጀንሲው በሕይወት ስለመኖር ማረጋገጥ የኤጀንሲው ሃላፊነት መሆኑ መታወቅ አለበት" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ ከዚህ በፊትም መገለጹን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካቶች መነጋገሪያ ሲያድርጉት መቆየቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ "ይህ ግን መታወቅ ያለበት የኤጀንሲው ሥራ መሆኑ ነው" ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ