ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች፤ ከታሕሳስ 21 ጀምሮ ሲሰጥ የቆየውን የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዘመቻ ለመውሰድ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

"በከተማዋ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ታዳጊ ሴት ልጆችን ለመከተብ አስቸጋሪ ካደረጉብን ነገሮች ውስጥ አንዱ ነበር" ብሏል፡፡

ወላጆች "ልጆቻችን ሕክምናቸውን የሚከታተሉት ሙሉ በሙሉ ውጪ ሀገር በመሆኑ ክትባቱንም ውጪ ነው" የሚከተቡት በሚል እንደሆነ፤ የቢሮው የክትባት አገልግሎት አስተባባሪ ሙሉቀን ተስፋዬ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ክትባቱ በዓመት አንድ ጊዜ ሲሰጥ የነበረ በመሆኑ ማህበረሰቡ ዘንድ እንደሌሎች ክትባቶች ነገሩን በደንብ የመረዳት ችግር እንደነበረ ገልጸው፤ በትምህርት ቤት ደረጃ "የኛ ልጆች ውጪ ነው የሚከተቡት" ካሉት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ውጪ ክትባቱን ለመውሰድ ያን ያህል የከለከሉ አለመኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ወላጆችንና የሀገር ውስጥ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶችን በአጠቃላይ ማህበረሰቡን ቀርቦ በማወያየት፤ ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡና ከበሽታው ለመጠበቅ ኃላፊነት እንዲወስዱ ከፍተኛ የሆነ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከታሕሳስ 21 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በዘመቻ መልክ ሲሰጥ በቆየው ክትባት፤ በተጨማሪ ሌሎች የማጣሪያ ቀናትን በመጠቀም እስካሁን 178 ሺሕ 660 ሴት ታዳጊዎች ክትባቱን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

ከነዚህ ውስጥ 174 ሺሕ 598 የሚሆኑት በትምህርት ቤት የተከተቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ጎዳና ላይ የሚኖሩ እንዲሁም ከከተማ ርቀው የሚገኙ ልጃገረዶችን ያካተተ ሥራ መሰራቱን አስተባባሪው አክለው ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ