ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክልሎች ውስጥ ያለው ጥቃት እየተባባሰ ባለበት ወቅት፤ የኮንጎ ጦር በኤም 23 አማፂ ቡድን ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ማግኘቱን አስታውቋል።

በሳምንቱ መጨረሻ የኮንጎ ጦር ከደቡብ ኪቩ የኤም 23 ሃይሎችን በተሳካ ሁኔታ በማስለቀቅ በሰሜን እና በደቡብ ኪቩ ግዛቶች የሚገኙ በርካታ ቁልፍ ከተሞችን መያዙ ተገልጿል።

ጦሩ በታጣቂ ሃይሉ ላይ እየወሰደው ባለው የማጥቃት ወታደራዊ ዘመቻ፤ ኪቩን ጨምሮ 5 ግዛቶችን ማስለቀቁን ገልጿል፡፡

የሰሜን ኪቩ ጦር ቃል አቀባይ ኮ/ል ንዲጂኬ ካይኮ ጉዩሉም፤ ጦሩ በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር የነበሩ በርካታ አካባቢዎችን እንደገና መቆጣጠሩን የገለጹ ሲሆን፤ ቀጣይነት ያለው የተኩስ አቁም ቢደረግም እንኳን፤ ወታደሮቹ ሰላማዊ ሰዎችን የመከላከል ሂደታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አፅንዖት መስጠታቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

ነገር ግን እራሱን ኤም 23 በሚል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም፡፡

በኮንጐ ጦር እና በኤም 23 አማፂያን መካከል ላለፉት በርካታ ሳምንታት ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በጎማ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ መንደሮች የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በብዛት የቱትሲ አማፂ ቡድን የሆነው ኤም 23 እንደኤሮፓዊያኑ በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንጎ ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን፤ ከሩዋንዳ ድንበር ላይ የምትገኘውን የጎማ ከተማን ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ከዛን ጊዜ አንስቶ ግጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ፤ ሀገሪቱን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከቷል።