ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትላትናው ዕለት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባዔው ያጸደቀው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ለታክስ ከፋዩ ሳይሆን ለታክስ አስከፋዩ የወገነ ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ የቋሚ ኮቴውን ሪፖርትና ውሳኔ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸውም፣ ረቂቅ አዋጁ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ገቢ በመሰብሰብ ለመሰረተ-ልማቶች እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ለማዋል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶም ከአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ሪፖርቱን እና የውሳኔ ሃሳቡን በመቃወም አስተያየት እና ጥያቄዎችን ቀርበዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም የምክር ቤት አባል እና የኦሎምፒክ ኮሚቴ ስብሳቢው ዶክተር አሽብር ወልደጊዮርጊስ በርካታ ጥያቄዎችን የጠየቁ ሲሆን፤ "ከቅጣት ጋር በተያያዘ እንደሀገር ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ ይታወቃል፤ ይህ ባለበት ሁኔታ በአምስት ቀናት ውስጥ ወደ ቅጣት ለመሄድ መታሰቡ ተገቢነት የለውም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ሀሳባቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባሉ እና የአብን ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ሲሆኑ፤ "አጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ካለው የታክስ ጫና አንፃርና መንግሥት አሁን ከደረሰበት ታክስ የመሰብሰብ አቅም በተጨማሪ፤ አዲስ የታክስ መሰብሰቢያ መንገድ አያስፈልገውም" ብለዋል፡፡

"የመንግሥት ታክስ የመንግሥትን ወጪ ለመመለስ ከሆነ ከ80 በመቶ በላይ ሄዷል" ያሉ ሲሆን፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ አዲስ የታክስ አዋጅ አስፈላጊነቱን ተቃውመዋል፡፡

ሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረገውም ንፅፅር በተመለከተ ተገቢ ያልሆነ ንፅፅር መሆኑን በማንሳት፤ በተለይም "የንፍስ ወከፍ ገቢያችን አነስተኛ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል" ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ እና የገቢ ምንጭን ያላገናዘበ፣ ለታክስ ከፋዩ ተደራራቢ ጫና የሚፈጥር መሆኑና ቋሚ ኮሚቴው ለታክስ ከፋዩ ሳይሆን ለታክስ አስከፋዩ ውግንና ያሳየበትን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡን ጠይቀዋል፡፡

በአዋጁ በተደነገገው መሰረት ለማንኛውም ንብረት የሚከፈለው ታክስ መጠን ከንብረቱ የገበያ ዋጋ ወይም ምትክ ዋጋ 25 በመቶ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን፤ ይህም በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል።

Post image

በጉባኤው ላይም የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴር የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ ሀሳባቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በተለይም ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱ ያሏቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሀሳባቸውም ገቢ አሰባሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ታምኖበት የተሰራ መሆኑን በማንሳት፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተነሳውን ሀሳብ በሚመለከት "ከዚህ በፊት ከተነሳው ሀሳብ ጋር የሚጣርስ ሀሳብ ተነስቷል" ብለዋል፡፡

ለምሳሌም ኢትዮጵያ በአግባቡ ታክስ እየሰበሰበች አይደለም እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይኑር የሚል ጥያቄ ሲነሳ መቆየቱን ያሳታወሱ ሲሆን፤ "ይህ አዲሱ የንብረትና ታክስ አዋጅ ይህንን ችግር የሚቀርፍ ነው" ሲሉም ለቅሬታ አንሺዎች ኢትዮጵያ የተሻለ ታክስ ሰብሳቢ ናት ተብሎ መነሳቱ ግር እንዳላቸው በመጠቀስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁን በአራት ተቃውሞ፣ በአስር ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጭ ድምጽ አጽድቆታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ