ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 ዓ.ም. ስድስት ወራት ውስጥ ከተቀመጠዉ መመሪያ ውጭ ሲሸጡ በተገኙ ከ95 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የትግራይ ክልል ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የፕላን ልማት እና እቅድ ክትትል ዳይሬክተር ሐጎስ ግርማይ፤ በተያዘው ግማሽ ዓመት ከ265 ሺሕ በላይ ቁጥጥር ለማድረግ የታቀደ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ መካከል 153 ሺሕ በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር የተደረገ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።
አክለውም ከተደረገው ቁጥጥር መካከል ከ58 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ጥፋት ያልተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከ95 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መመሪያዎችን የጣሱና በተለያዩ ጥፋቶች የተገኙ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም እንደየጥፋታቸው መሠረት እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ያለ ንግድ ፈቃድ መስራት፣ ባልተመዘገበ አድራሻ መስራት፣ ንግድ ፈቃድ ሳያድሱ በሚሰሩ እንዲሁም ከተቀመጠው የዋጋ ዝርዝር ውጭ በሚሸጡ ነጋዴዎች የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 40 የሚሆኑት በሕግ እንዲጠየቁ የተደረገ ሲሆን፤ ሌሎች የንግድ ተቋማት ደግሞ እንዲታሸጉ፣ የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ፣ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው እንዲሁም ተደጋጋሚ የሆነ ጥፋት ከሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ በመውሰድ እዲቀጡ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።
ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ እና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ከሚመለከተዉ አካል ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ