መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሁኑ ወቅት ሕገ-ወጥ የወባ መድኃኒት ስርጭቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።

ከጊዜ ወዲህ ሕገ-ወጥ የወባ መድኃኒት ስርጭት ላይ ተሳትፈው የሚቀጡ ሰዎችና የሚደረገው ቁጥጥሩም እየበዛ ትኩረት ተሰጥቶበት ስለመጣ፤ በተወሰደ የተጠናከረ እርምጃ ሕገ-ወጥነቱ ሊቀንስ የቻለበት ሁኔታ ስለመኖሩ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቅርንጫፍ ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወንዱ ቀጠለ ለአሐዱ ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር የሚስፋፋት መንገድ አንዱ ፍላጎቱ ከመጨር ጋር ተያይዞ የሚመጣ መሆኑን በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት የወባ በሽታ ስርጭቱም የመቀነስ አዝማሚያ እንዳለው ተናግረዋል።

Post image

በተለይም ባለፈው ዓመት ግን የወባ በሽታ ስርጭት ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ በርካታ ሕገ-ወጥ የመድኃኒት አዘዋዋሪዎች የወባ መድኃኒትን መንግሥት ከሚያቀርበው በላይ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በኮንትሮባንድ መልኩ ለማስገባት ሲሞክሩ መያዛቸውንና ምርታቸውም እንዲወገድ መደረጉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በሕጋዊ መንገድ በመንግሥት ሆስፒታል ከገቡ በኋላም መድኃኒቶቹ እንዲቀየሩ ተደርጎ ወደ ግል ፋርማሲዎች የሄዱበት አጋጣሚዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

በመሆኑም ከክልል ጤና ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን በርካታ ፋርማሲዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ በመግለጽ፤ እዚህ ላይ የተሳተፉ ድርጅቶችን ፈቃዳቸው መሰረዙንና ግለሰቦች ላይ ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው ከተፈረደባቸው በተጨማሪ ክሳቸው ገና በሂደት ላይ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

አሐዱም በየጊዜው የሚያዙ ሕገ-ወጥ የወባ መድኃኒቶችን ቁጥራዊ መረጃ የጠየቀ ሲሆን፤ ሥራ አስፈፃሚው በምላሻቸው "ሕገ-ወጥ መድኃኒቶች በተለያየ ኬላና በርካታ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚገቡ በመሆናቸው ምን ያክል ቁጥር እንዳላቸው ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።

አክለውም ዋጋቸውን በሚመለከትም እነዚህ መድኃኒቶች በኢትዮጵያ ያልተመዘገቡና አምራቾቹም የማይታወቁ በመሆናቸው ግምታዊ እንጂ ትክክለኛ ዋጋቸውን ለማውጣት እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም ሕገ-ወጥ የወባ መድኃኒት ስርጭቱን ለመግታት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ሕብረተሰቡም ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ