መጋቢት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዜጎች ላይ የጤና ችግር ሊያመጡ በሚችሉ የታሸጉ የውሃ መጠጥ ምርቶች ባላቸው ይዘት እና የምርት ጥራት ዙሪያ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባ፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በዘርፉ አምራቾች ላይ የምርታቸውን ይዘት ጥናት ማከናወን፤ በሌብሊንግ ወይም የምርቱን ገላጭ ጸሁፍ አመሳስሎ የመጠቀም ሁኔታን ለማስቀረት ይረዳል ብሏል፡፡

በንግድ እና በቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፋብሪካ ምርቶች ተቆጣጣሪ አንዷለም ክንዴ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ የምርቱ ይዘት በተመለከተ ስለምርቱ መግለጫ ጹሁፍ የሌለው ምርት ገበያ ላይ ማዋል ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በምርቶች ማሸጊያ ላይ የሚገኙ ስለ ምርቱ የሚገልጹ ዝርዝር መረጃዎች በተመለከተ የቁጥጥር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አንድን ምርት ለመለየት ብሎም የተመረተበትን ተቋም ምንነት እና አድራሻ ለማወቅ በምርቶች ላይ የሚኖር ገላጭ ጽሁፍ ወይም ሌብሊንግ ማስቀመጥ፤ እራሱን ችሎ የተቀመጠ መስፈርት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

"እንደ ሀገር ጥቅም ላይ የሚውለው ውሃ የሚኒራል መጠኑን እንዲሁም የዜጎችን ጤና ከማስጠበቅ አንጻር 'ምርቱን መጠቀም የሚችሉ እና መጠየቀም የማይችሉ' ተብሎ ለመለየት፤ 'በታሸገ ውሃ ውስጥ ያለውን የጨው ይዘት ምን ያህል ነው?' የሚለውን በሌብሊን ወይም በምርቱ ገላጭ ጽሁፍ ላይ መቀመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

"ይህ መገለጫ ፅሁፍ ጠቀሜታው ከጥራት ጋር የተያየዘ ብቻ አይደለም" የሚሉት ተቆጣጣሪው፤ ከጥራት በላይ ስለ አንድ ምርት ለተጠቃሚው መረጃ የሚሰጥ ከዛም ባለፈ ስለአምራቹ ድርጅትም ጭምር መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የፋብሪካ ምርቶች ተቆጣጣሪ አንዷለም ክንዴ አክለውም፤ በተከናወነ የፍተሻ ሂደት ላይ ከተወሰዱ ናሙናዎች መካከል የደረጃ ምዘና መስፈርት አሟልተው ያልተገኙ የጃር ውሃ ማሸጊያዎች ስለመኖራቸው ለአሐዱ ተናግረዋል።

በአምራቾች ዘንድ ከደህንነት መስፈርት ጋር በተያያዘ የተለያየ ጉድለቶች እንደሚያስተውሉም ጨምረው ጠቁመዋል።

ግለሰቦች የጃር ውሃ ማሸጊያን ከውሃ በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንንም መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረግበት አሰራር ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡

በጃር ውሃ ምርት ላይ ምልክት ወይም ስለ ምርቱ የሚገልጽ፤ መለያ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ እንደ ክፍተት የሚነሳ ጉዳይ ስለመሆኑ ተነግሯል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ